Wednesday, February 17, 2010

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 1

ምዕራፍ 1።

1፤ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው።

2፤ ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ።

3፤ ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታ መስገጃ ሄዱ።

4፤ ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር።

5፤ የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር።

6፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

7፤ በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ።

8፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው። ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል።

9፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና።

10፤ አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና።

11፤ እግዚአብሔርም ሰሎሞንን። ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤

12፤ ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው።

13፤ ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።

14፤ ሰሎሞንም ሰረገሎቹንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።

15፤ ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።

16፤ ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።

17፤ አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 2

ምዕራፍ 2።

1፤ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ አሰበ።

2፤ ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ።

3፤ ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ። ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ሰደድህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ።

4፤ እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘላለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራና እቀድስ ዘንድ አሰብሁ።

5፤ አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው።

6፤ ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

7፤ አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ።

8፤ ደግሞም ባሪያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ስደድልኝ።

9፤ የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር ይሆናሉ።

10፤ እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።

11፤ የጢሮስ ንጉሥም ኪራም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ ብሎ ለሰሎሞን መልእክት ላከ።

12፤ ኪራምም ደግሞ አለ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን።

13፤ አሁንም ከብልሃተኞችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ኪራምአቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ሰድጄልሃለሁ።

14፤ እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩንም፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅርጽም ሌላም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ያውቃል።

15፤ አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባሪያዎቹ ይስደድ፤

16፤ እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንሰድዳለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።

17፤ ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ።

18፤ ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 3

ምዕራፍ 3።

1፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።

2፤ በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መሥራት ጀመረ።

3፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው ስፍር ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ።

4፤ በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው።

5፤ ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት።

6፤ ቤቱንም በዕንቍ አስጌጠው፤ ወርቁንም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ።

7፤ ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ፤ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ።

8፤ ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው።

9፤ የምስማሮቹም ሚዛን አምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ።

10፤ በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱ ኪሩቤልን ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው።

11፤ የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።

12፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር።

13፤ የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር።

14፤ ከሰማያዊውም ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት።

15፤ በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጕልላት አምስት ክንድ ነበረ።

16፤ እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በአዕማዱ ራስ ላይ አደረጋቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው።

17፤ አዕማዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፤ በቀኝም የነበረውን ስም ያቁም በግራም የነበረውን ስም በለዝ ብሎ ጠራቸው።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 4

ምዕራፍ 4።

1፤ ደግሞም ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም አሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ።

2፤ ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ።

3፤ በበታቹም ለአንድ ክንድ አሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር።

4፤ በአሥራ ሁለትም በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን ሦስቱም ወደ ምዕራብ ሦስቱም ወደ ደቡብ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበር፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ።

5፤ ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር።

6፤ ደግሞም አሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር።

7፤ አሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው።

8፤ አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ።

9፤ ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፥ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ።

10፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።

11፤ ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።

12፤ ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ።

13፤ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መርበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ።

14፤ መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥

15፤ አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን አሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ።

16፤ ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ።

17፤ ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው።

18፤ ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር።

19፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥

20፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ።

21፤ አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ።

22፤ ጕጦቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 5

ምዕራፍ 5።

1፤ እንዲሁም ሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን የብርና የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰሎሞን አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አኖረው።

2፤ በዚያን ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች ሁሉ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

3፤ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተከማቹ።

4፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፥ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሡ።

5፤ ታቦቱንም የመገናኛውንም ድንኳን በድኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ።

6፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በታቦቱ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር።

7፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በቅድስት ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት።

8፤ ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፥ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር።

9፤ መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅዱስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ።

10፤ በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም።

11፤ በዚያም የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፥ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር፤

12፤ መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፥

13፤ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ። እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው።

14፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 6

ምዕራፍ 6።

1፤ ሰሎሞንም። እግዚአብሔር። በጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል፤

2፤ እኔ ግን ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ ማደሪያ ቤትን ሠራሁልህ አለ።

3፤ ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር።

4፤ እርሱም አለ። ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤

5፤ እርሱም። ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤት በዚያ ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥሁም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም፤

6፤ ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ ብሎአልና።

7፤ አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አስቦ ነበር።

8፤ እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን። ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ መልካም አደረግህ።

9፤ ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም አለው።

10፤ እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ።

11፤ ከእስራኤልም ልጆች ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ።

12፤13፤ ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፥ በላዩም ቆመ፥ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹንም ዘርግቶ እንዲህ አለ።

14፤ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥

15፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቀህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።

16፤ አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ። አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ ይሄዱ ዘንድ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ።

17፤ አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለዳዊት የተናገረኸው ቃል ይጽና።

18፤ በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን?

19፤ ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ባሪያህም በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ።

20፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ። በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ።

21፤ ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

22፤ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥

23፤ በሰማይ ስማ፥ አድርግም፥ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፥ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው።

24፤ ሕዝብህም እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ስማ፥

25፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጥሃት ምድር መልሳቸው።

26፤ አንተን ስለ በደሉ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፥

27፤ የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ።

28፤ በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥

29፤ ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ ማናቸውም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥

30፤31፤ ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው።

32፤ ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ ስለ ብርቱውም እጅህ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥

33፤ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።

34፤ ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥

35፤ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው።

36፤ የማይበድል ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር ቢማርኩአቸው፥

37፤ በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም አገር ሳሉ ተመልሰው። ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥

38፤ በተማረኩበትም በምርኮአቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥

39፤ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን ይቅር በል።

40፤ አሁንም፥ አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዓይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮችህም የሚያደምጡ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ።

41፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ከኃይልህ ታቦት ጋር ወደ ዕረፍትህ ተነሣ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው።

42፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ ለባሪያም ለዳዊት ያደረግህለትን ምሕረት አስብ።

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 7

ምዕራፍ 7።

1፤ ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ።

2፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም።

3፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ። እርሱ መልካም ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና ብለውም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

4፤ ንጉሡም ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።

5፤ ንጉሡም ሰሎሞን ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ።

6፤ ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር።

7፤ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩን ውስጥ ቀደሰ፤ ሰሎሞንም የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ስቡንም መያዝ አልቻለምና የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ስብ በዚያ አቀረበ።

8፤ ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆኑ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያሉ እስራኤል ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

9፤ ሰባት ቀንም መሠዊያውን ቀድሰው፥ ሰባት ቀንም በዓል አድርገው ነበርና በስምንተኛው ቀን የተቀደሰውን ጉባኤ አደረጉ።

10፤ በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛውም ቀን ሕዝቡን ወደ ድንኳናቸው አሰናበተ፤ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ደስ ብሎአቸው ሐሴትን እያደረጉ ሄዱ።

11፤ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ።

12፤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ።

13፤ ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥

14፤ በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈግሉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።

15፤ አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ።

16፤ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።

17፤ አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንደ ሄደ በፊቴ ብትሄድ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ብትጠብቅ፥

18፤ ከአባትህ ከዳዊት ጋር። በእስራኤል ላይ አለቃ፥ የሚሆን ከዘርህ አይታጣም ብዬ ቃል ኪዳን እንዳደረግሁ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።

19፤ እናንተ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትተዉ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥

20፤ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላችኋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፥ በአሕዛብም ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት አደርገዋለሁ።

21፤ ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውንም ይህን ቤት እያዩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ? ብለው ይደነቃሉ።

22፤ መልሰውም። ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።